Fana: At a Speed of Life!

መካከለኛና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአዳዲስ ፈጠራና ሥራ ፈጣሪዎች ትኩረት መስጠት አለባቸው–ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመካከለኛ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአዳዲስ የፈጠራና ሥራ ፈጣሪዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል አሳሰቡ።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት ፈጠራና ሥራ ፈጣሪዎች” ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሚኒስትሯ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ወቅቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂና አሰራር ለማፍለቅ ለሚያስችል የፈጠራ ስራና ሥራ ፈጣሪዎች ትኩረት የሚሰጥበት ነው።

መንግስት ዘርፉን የሚመራ ተቋም ከማቋቋም ጀምሮ ፖሊሲ በመቅረጽ እና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ፈጠራንና ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የመካከለኛና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዳዲስ ፈጠራን በማበረታታትና ልዩ ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን መስራት የሚችሉበት መልካም አጋጣሚ መፈጠሩን ገልጸዋል።

በመሆኑም ተቋማቱ ይህን የጀመሩትን ተግባር በቀጣይም ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

“በተጨማሪም መንግስታዊ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማትም ለፈጠራ ሥራ ማደግ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ሥራው ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የሚያስመሰግነው ነው” ብለዋል ሚኒስትሯ።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለፈጠራ ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በፈጠራ የተካኑ ባለተሰጥኦዎችን በማሰልጠን እራሳቸውንና ሀገራቸውን ተወዳዳሪና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዜጎችን እያፈራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በፈጠራና ሥራ ፈጣሪዎች ላይ አተኩሮ ለሁለት ቀን እየተካሄደ ባለው የውይይት መድረክ የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.