Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያንና ደቡብ ኮሪያን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ጉባኤ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የንግድና የኢንቨስትመንት ጉባኤ በደቡብ ኮርያ ቡሳን ተካሂዷል።

በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም የኮሪያ-ኢትዮጵያ የንግድ ማህበር በተዘጋጀው የኢንቨስትመንትና የንግድ ጉባኤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር የንግድ ለንግድ ትስስሩን ለመገንባት ያለመ ነው ተብሏል።

በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ÷በጉባኤው በሁለቱ ሀገራት መካከል ጠንካራ የሆነ ታሪካዊ ግንኙነት መኖሩን አስታውሰው ግንኙነቱ ወደ ላቀ የኢንቨስትመንት ትስስር ማደግ ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የተደረገው ሪፎርም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተው በኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ ባለ ሀብቶችን ለማገዝ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዋናው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉባኤ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ ከሚፈልጉ ደቡብ ኮሪያውያን ባለሀብቶች ጋር የንግድ ለንግድ ውይይቶችም መደረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.