Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ቻድ በአቪዬሽን ዘርፍ በትብብር ለመሥራት ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ቻድ በአቪዬሽን እና በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ሁለቱ ሀገራት ስምምነቱን የተፈራረሙት በካናዳ ሞንትሪያል እየተካሄደ ከሚገኘው 41ኛው የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ጉባዔ ጎን ለጎን በነበራቸው መርሐ ግብር መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ እና የቻድ የሲቪል አቪየሽን እና የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ሚኒስትር ሂሴን ጣሂር ሱጉሜ ተገኝተዋል፡፡

በሁለትዮሽ የአቪየሽን አገልግሎት ላይም ፍሬያማ ውይይት አድርገው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተመላክቷል፡፡

ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በቻድ መካከል ያለውን የአቪዬሽን ዘርፍ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መንገድ የሚከፍት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በስምምነቱ ላይ የቻድ የሲቪል አቪየሽን እና የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ሚኒስትር እንዳሉት÷ ከኢትዮጰያ ጋር በአየር ትራንስፖርት ቁጥጥር እና በደኅንነት ሥርዓቶች ላይ በጋራ ለመስራት እና ቀደም ሲል የነበረንን ግንኙነት ለማጠናከር ስምምነቱ ላይ መደረሱ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

እየተካሄደ ከሚገኘው ጉባዔ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር በአቪዬሽንና በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን እየፈጸመች ትገኛለች ተብሏል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.