የዘንድሮ ኢሬቻ ወደ አዲስ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት እና በድል ላይ ድል የምናስመዘግብበት እንዲሆንልን እመኛለሁ -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮ ኢሬቻ ወደ አዲስ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት እና በድል ላይ ድል የምናስመዘግብበት እንዲሆንልን እመኛለሁ ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፥ እንደ ኢሬቻ ያሉ ታላላቅ ክብረ በዓላትን እንደ አንድነታችን ማጠናከሪያ መሣሪያ ይዘን በአጭርና በረዥም ጊዜ የያዝነውን የብልፅግና ጉዟችንን ለማደናቀፍ የተከፈተብንን ዘመቻዎች ሁሉ ጥሰን በማለፍ የያዝነውን ራዕይ ለማሳካት በአንድነት እንድንሠራ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
በታሪክ ውስጥ በአንድነት እንጂ በልዩነት ተከብረን፣ ተፈርተንም ሆነ አሸንፈን አናውቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አንድ ሆነን ስንቆም በሁሉም ግንባር ድልን እንደምንጎናጸፍ አይተናል፥ የትኛውንም የሚሸረብብንን ሤራ ማክሸፍ እንደምንችልም በተጨባጭ አሳይተናል ብለዋል።
አሁንም ነጻነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተኑ ጠላቶች እንዳሉ ጠቁመው፥ ከመንገዳችን ግን ሊያሰናክሉን አይችሉም ነው ያሉት።
የሥራ ባህላችንን በማሻሻል በሁሉም የልማት መስኮች ተሠማርተን ለማሸነፍ በቁጭት መትጋት እንዳለብንም አሳስበዋል።
ችግርን የመቋቋም አቅማችን በንቃታችን ተደራጅተን አንድነታችንን በጠበቅንና በተጨባጭ ሠርተን ባሳየነው ልክ በችግርና በፈተና ጊዜ ካሳለፍነው ልምዳችን ተምረናል ሲሉም አክለዋል።
“የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን ከክረምቱ ወደ ብርሃናማው መጸው ተሸጋገራችሁ፤ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
እንኳን ለኢሬቻ በዓል አደረሳችሁ
የገዳ ሥርዓት ባለቤት የሆንከው የተከበርከው የኦሮሞ ሕዝብ፤
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን ከክረምቱ ወደ ብርሃናማው መጸው ተሸጋገራችሁ፤ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች እንዲሁም ከትንሽ እስከ ትልቅ ጠላቶቻችን የደቀኑብንን አደጋ አሳልፎ ለመጸው ብርሃን ላበቃን ፈጣሪ ምስጋና ይግባው፡፡ ኦሮሞ ከገዳ ሥርዓት በወረሰው ዕሴት ክረምት አልፎ መጸው ሲገባ ፈጣሪውን ያመሰግናል፡፡
የክረምቱን ጨለማ አሳልፈህ፣ እህልን አብቅለህ፣ ማሳውን አሳምረህ የመጸውን ንጋት ስላሳየሀን ፈጣሪ ምስጋና ይግባህ ይላል፡፡ርጥብ ሣር ይዞም “መሬሆ” “መሬሆ” እያለ ወደ መልካ በማቅናት የኢሬቻ ሥርዓትን ይከውናል፡፡
ኢሬቻ ክረምት አልፎ መጸው ሲገባ ፈጣሪ የሚመሰገንበት በታላቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበር ነው፡፡ በድጋሚ የኦሮሞ ሕዝብን፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብን እንኳን አደረሳችሁ ስል ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ኢሬቻ የሰላም መድረክ ነው፡፡
ለኢሬቻ ወደ መልካ የሚሄዱ ርጥብ ሣር በእጃቸው ይዘው የኢሬቻ ሥርዓትን ከመከወናቸው በፊት ሦስት ጥያቄዎችን መመለስ አለባቸዉ፡፡ የገዳ አባቶች “በመካከላችሁ ሰላም አለ?” “ለፈጣሪስ ሰላማዊ ናችሁ?” “ከተፈጥሮስ ጋር ሰላም ናችሁ?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡
ወደ መልካ ለኢሬቻ የሄደው የበዓሉ አክባሪም መልካውን በርጥብ ሣር ከመንካቱ በፊት ሰላም ነው ብሎ ይመልሳል፡፡
ከዛም በርጥብ ሣሩ መልካውን ነክቶ “መሬሆ” “መሬሆ” በማለት ፈጣሪውን ያመሰግናል፡፡ ለዚህም ኢሬቻን የሚያውቅ ሰው ቂምና በቀልን ትቶ ሰላምን ይሰብካል፡፡
አንድነትና ሰላምን ትብብርና ወንድማማችነትን ያጠናክራል፡፡ ከፈጣሪ ላገኘው የከበረ ስጦታ ዕውቅና ይሰጣል፡፡ በተፈጥሮ ያለውን መስተጋብርና ትብብር እያደነቀ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል፡፡
ልምላሜን የፈጠረ አምላክ ከሰው ልጅ ምስጋና ያገኛል፡፡
የሰው ልጅ ፈጣሪ የሰጠውን ርጥብ ሣር ይዞ ተፈጥሮን ያደንቃል ፈጣሪን ያመሰግናል፡፡
ኢሬቻን የሚያከብር ከራሱ፣ ከጎረቤቱ፣ ከውስጥና ከውጪ በሀገሩ እና ሩቅ ላለው ሰው ሰላማዊ መሆን አለበት፡፡ ለኢሬቻ የሚሄድ ሰው ጥላቻን ትቶ ዕርቅ ማውረድ አለበት ከኢሬቻ ሲመለስም ቂምና ጥላቻን እንዲሁም ያለፈ ጉዳትን ከማስታወስ ራሱን መቆጠብ አለበት፡፡
ኢሬቻን ማክበር በጋራ ምስጋናን ማቅረብ ነው፡፡
የተፈጥሮ ሕግ እንዳይስተጓጎል ፈጣሪ በፍጡራን እንዳያዝን ፈጣሪን መለመን ነው፡፡
ስለዚህ ኢሬቻ ዕርቅ ነው፡፡ ሰላም ነው ፍቅርና አንድነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የገዳ ሥርዓት ባህልና ዕሴት ነው፡፡
ኢሬቻ የንጽሕና መድረክ ነው፡፡
ኢሬቻ በሐሳብ መንጻትን ይፈልጋል፡፡
ቂም መያዝና ስም ማጥፋት ከኢሬቻ ዕሴቶች ተቃራኒ ናቸው፡፡ ለኢሬቻ የሚሄድ ሰው ይቅር ባይ የሆንከው ፈጣሪ በማለት እጁን ዘርግቶ አምላኩን ይለምናል ያመሰግናል፡፡
በኢሬቻ ሰማይና ምድርን የፈጠረ አምላክ ይመሰገናል፡፡ሐቅን ማዛባት እውነትን መደበቅ ነውር እንደሆነ ይሰበካል፡፡ የተፈጥሮና የፍጡራን ሕግ የሚታወቅበት ነው፡፡
የመጸው ወቅት የፈጣሪ የእጅ ሥራ የሚደነቅበት ነው፡፡
ከጨለማ ምዕራፍ ወደ ብርሃን ከክረምት ወደ መጸው ከቡቃያ ወደ አዝመራ የምንሸጋገርበትም ነው፡፡
ይህን የፈጣሪ ሥራ የሆነውን የተፈጥሮ ኡደትን “መሬሆ” “መሬሆ” በማለት የሚደነቅበት የኢሬቻ በዓል የብርሃንና የምርቃት ቀን ነው፡፡
ኢሬቻ የወንድማማችነት/ እኅትማማችነትና የአንድነት ቀን ነው፡፡
በገዳ ሥርዓት በጋራ ሠርቶ በጋራ መመገብ መተባበርና አብሮ መቆም ለሐቅ መታገልና በችግር ጊዜ መረዳዳት የገዳ ሥርዓት የቀደመ ባህል ነው።
ኢሬቻ አንድነትና ወንድማማችነት/እኅትማማችነት የሚጠነክርበት ነው። ኅብረት የሚጠነክርበት የፍቅር የወዳጅነት በጋራ የመኖር ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው።
ይህ ትልቅ ዕሴት የሰው ልጆችን ሁሉ እኩል ማየትና ማክበር በመቅረብ መረዳትን የሚያስተምር ነው። ስለዚህ የበዓሉ አክባሪ ይህን የኢሬቻ ሥርዓትን በማክብር ፈጣሪን ያመሰግናሉ።
ኢሬቻ በዘር በጾታ እና በእድሜ በሃይማኖትና በየትኛውም መሥፈርት ሰውን አይከፋፍልም። ለዚህም ነው ዛሬ ላይ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት የሚያከብሩት በዓል የሆነው። ለዚህም ነው ከኢትዮጵያውያን አልፎም የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን መሳብም የቻለው።
እኛ እንደ ሀገር እና ህዝብ የባህልና ወግ ባለፀጎች ነ፤ የሃይማኖት መቻቻል እና አብሮ መኖርን የሚያጠናክሩ የባህል ሥርዓቶች አሉን። አንዳችን የአንዳችንን ጉድለት ከመፈለግ ይልቅ መደማመጥን ያበረታታል ቂምና ጥላቻን ከመዘመር ሰላምና እውነትን መውደድን ያጠናክራል።
የዘፈቀደ እና የስንፍና ኑሮ የኛ አይደለም።
ለሁሉም ነገር ሕግ አለን።በሥርዓትና ወግ ለመኖር እንገደዳለን፤ጀግንነት እንጂ ክህደት እኛን አይገልጸንም ።
በታሪክ ውስጥ በአንድነት እንጂ በልዩነት ተከብረን ተፈርተንም ሆነ አሸንፈን አናውቅም። አንድ ሆነን ስንቆም በሁሉም ግንባር ድልን እንደምንጎናጸፍ አይተናል የትኛውንም የሚሸረብብንን ሤራ ማክሸፍ እንደምንችል በተጨባጭ አሳይተናል።
ያለፈው አራት አመት ልምዳችንም ይህንኑ ነው የሚገልጸው። ጠላቶቻችን ወድቀዋል ሲሉን ተነስተን ፈርሰዋል ሲሉን ተገንብተን አይተውናል። አሁንም ብዙ ነጻነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተኑ አሉ፤ ከመንገዳችን ግን ሊያሰናክሉን አይችሉም።
ሐቅ አለን፤ እውነት ላይ ቆመን እንታገላለን ፈጣሪም ከኛ ጋር ነው። ለየትኛውም ምድራዊ ኃይል አንንበረከክም። ትልቁ ጠላታችን የሆነውን ድህነት ለማሸነፍ መሥራት ይገባናል።
የሥራ ባህላችንን በማሻሻል በሁሉም የልማት መስኮች ተሠማርተን ለማሸነፍ በቁጭት መትጋት አለብን። ችግርን የመቋቋም አቅማችን በንቃታችን ተደራጅተን አንድነታችንን በጠበቅንና በተጨባጭ ሠርተን ባሳየነው ልክ በችግር በፈተና ጊዜ ካሳለፍነው ልምዳችን ተምረናል።
እንደ ኢሬቻ ያሉ ታላላቅ ክብረ በዓላትን እንደ አንድነታችን ማጠናከሪያ መሣሪያ ይዘን በአጭርና በረዥም ጊዜ የያዝነውን የብልፅግና ጉዟችንን ለማደናቀፍ የተከፈተብንን ዘመቻዎች ሁሉ ጥሰን በማለፍ የያዝነውን ራእይ ለማሳካት በአንድነት እንድንሠራ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
የዘንድሮ ኢሬቻ ወደ አዲስ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት እና በድል ላይ ድል የምናስመዘግብበት እንዲሆንልን እመኛለሁ።
ዓመቱ የስኬትና የድል ይሁንልን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 20፣ 2015 ዓ.ም