በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መክፈቻ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማና ባሕር ዳር ከተማ አሸነፉ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መክፈቻ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማና ባሕር ዳር ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ የውድድር ወቅቱን በድል ጀምረዋል።
ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተጀምሯል።
በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ አምበሉ ጌታነህ ከበደ በ50ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ድንቅ የቅጣት ምት ግብ፥ አርባምንጭ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በሌላኛው ጨዋታ የባሕር ዳር ከተማው ጣና ሞገድ ከመመራት ተነስቶ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በድጋሚ የተመለሰውን ኢትዮ-ኤሌትሪክን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ዱሬሳ ሹቢሳና ተስፋዬ ታምራት ለጣና ሞገድ ግቦቹን ከመረብ አሳርፈዋል።
ስንታየሁ ዋለጩ ለኢትዮ-ኤሌትሪክ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።
በሊጉ የአንደኛ ሳምንት መርሐ ግብር መሰረት ቅዳሜ ኢትዮጵያ መድን ከቅዱስ ጊዮርጊስ 7 ሰዓት ላይ የሚጫወቱ ሲሆን፥ ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና 10 ሰዓት ላይ ይጋጠማሉ፡፡