አቶ ደስታ ሌዳሞ በአፍሪካ ሀገራት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የተመራ ልዑክ በ2ኛው የአፍሪካ ሀገራት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጉባዔ ላይ በናይጄሪያ አቡጃ እየተሳተፈ ነው፡፡
ጉባኤው በአፍሪካ ከተሞችና ክልሎች መካከል በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በከተሞችና በኢንዱስትሪ ልማት ዙሪያ የተሻለ ትስስር በመፍጠር በአፍሪካ የተሻለ እድገትና ብልፅግና ለማምጣት ያለመ ነው ተብሏል።
ጉባኤው እየተካሄደ ያለው በአህጉር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ከሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም በልማት ዙሪያ የተቀመሩ ምርጥ ተሞክሮዎች እናጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበትና መሪዎቹ እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ እንደሆነም ተገልጿል።
በጉባዔው የሀገር መሪዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሆኑ የንግድ ኩባንያዎች ታድመዋል ነው የተባለው።