“ሆረ ፊንፊኔ” የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ሆረ ፊንፊኔ” የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እየተከበረ ነው።
በዓሉ በአዲስ አበባ አውደ ርዕይ፣ የፓናል ውይይት እና በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየ ሲሆን፥ በዛሬው እለትም “ሆረ ፊንፊኔ” ኢሬቻ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች እና ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል።
በተጨማሪም የመዲናዋ ነዋሪዎችና ከፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተውጣጡ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ ላይ ተገኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢሬቻ በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፥ እንደ ኢሬቻ ያሉ ታላላቅ ክብረ በዓላትን እንደ አንድነታችን ማጠናከሪያ መሣሪያ ይዘን፥ በአጭርና በረዥም ጊዜ የያዝነውን የብልፅግና ጉዟችንን ለማደናቀፍ የተከፈቱብንን ዘመቻዎች ሁሉ ጥሰን በማለፍ የያዝነውን ራዕይ ለማሳካት በአንድነት እንድንሠራ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
በታሪክ ውስጥ በአንድነት እንጂ በልዩነት ተከብረን፣ ተፈርተንም ሆነ አሸንፈን አናውቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አንድ ሆነን ስንቆም በሁሉም ግንባር ድልን እንደምንጎናጸፍ አይተናል፥ የትኛውንም የሚሸረብብንን ሤራ ማክሸፍ እንደምንችልም በተጨባጭ አሳይተናል ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ÷የምስጋና፣ የሰላምና የይቅርታ መገለጫ የሆነውን ኢሬቻን ስናከብር ለሀገር ሰላምና ልዕልና አካልና ህይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡