Fana: At a Speed of Life!

የወንድማማችነት መሰረቶችን በማስፋት የአፍሪካን ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የወንድማማችነት መሰረቶችን በማስፋት በተለያዩ ዘርፎች የአፍሪካን ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ገለጹ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና የወንድማማችነት ሁነት በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ተካሄዷል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ÷ የወንድማማችነት መሰረቶችን በማስፋት በተለያዩ ዘርፎች የአፍሪካን ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የፓን አፍሪካኒዝምን ጽንሰ ሀሳብ ለአዲሱ ትውልድ በማስተማር የትስስር መሰረት ሊሆን እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ ችግር የሆነውን የዓየር ንብረት ለውጥ እና የሚያስከትለውን ችግር ለመፍታት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊስ በመተግበር ውጤታማ ተግባር ተከናውነዋልም ነው ያሉት፡፡

የፓን አፍሪካ እሳቤን ለመጪው ዘመን መሪዎች ማስተማር እና የጋራ እሴቶችን ማጠናከር የወደፊት አፍሪካን ለማስተሳሰር መሰረት ነው ብለዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፍስሃ ሻውል በበኩላቸው÷የዚህ ሁነት አላማ የፓን አፍካኒዝም ፅንሰ ሀሳብ ታሪክን በድጋሚ በማደስ የፖለቲካ ነፃነት እንደተገኘው በሌሎች ዘርፎችም ማሳካት እንደሚገባ ለማሳየት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ማቲኮ ሊቲሴ÷ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ለነፃነት ያደረጉትን ትግል በመደገፍ ኢትዮጵያ የነበራት ሚና ትልቅ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.