Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የሆረ ፊንፊኔ ” የኢሬቻ በዓል ባማረና በደመቀ መልኩ በሰላም መከበሩን አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የተከበረው “የሆረ ፊንፊኔ ” የኢሬቻ በዓል ባማረና በደመቀ ባህላዊ እሴቱንና ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

ለ4ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ በተከበረው በዓል በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ መሳተፉን ያነሱት ከንቲባ አዳነች፥ በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ ባማረ ድባብ፣ በከፍተኛ ድምቀትና ውበት፣ በእንግዳ ተቀባይነት ስሜት ባህላዊ እሴቱንና ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ከመቼውም ጊዜ በላይ  በጋራ ተከብሯል ብለዋል።

በበዓሉ ላይ ትብብራችን ጎልቶ የወጣበት፣ ኢትዮጵያዊ አብሮነትንና ኅብረብሄራዊነት ደምቆና ፈክቶ ድንቅ የበዓል አከባበር የታየበት እንደነበርም አንስተዋል።

አሸባሪ ቡድኖች በቀቢፀ ተስፋ በጦር ሜዳ የደረሰባቸውን ኪሳራ ለማካካስ በከተማችን የተከበረው  የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የሁከት ማዕከል ለማድረግ በተጨባጭ  ቢንቀሳቀሱም፥ በሰላም ወዳዱ ህዝብ፣ በፀጥታ ሃይሎችና ህዝባዊ ሰራዊታችን እንዲሁም በአመራሩ ቅንጅትና ትብብር የጥፋት ህልማቸውን በማክሸፍ ሰላማዊና  የተረጋጋ በዓል ማክበር ተችሏል ነው ያሉት።

በዓሉ ስኬታማ እና ያማረ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ዋናውንና የማይተካ ሚና ለተጫወተው የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብም ምስጋና አቅርበዋል።

አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ቄሮዎች፣ ቀሬዎች እና ፎሌዎች ይህ በዓል እሴቱንና ስርዓቱን ጠብቆ በከፍተኛ ድምቀትና በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር ላደረጉት አስተዋጽኦም አመስግነዋል።

ከዚህ ባለፈም በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በበቂ ዝግጅትና በሀላፊነት ስሜት በብቃት ለሰሩ የከተማዋ የጸጥታ አካላት፣ የሰላም ሰራዊት አባላት እንዲሁም የደንብ ማስከበር አገልግሎትም ምስጋና አቅርበዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችም ሃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ለበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ ላደረጉት አስተዋጽኦ እንዲሁም በዓሉን ለመታደም ወደ ከተማዋ የመጡ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓሉ የጋራ መሆኑን በተግባር በማረጋገጥ ላሳዩት ታላቅ የአብሮነት ተምሳሌትነት ምስጋና ይድረሳችሁ ብለዋል።

የበዓሉን መልካም ገፅታ እና የህዝቡን አብሮነት አጉልተው ላሳዩ የሚዲያ ተቋማትና የሚዲያ ባለሙያዎች ምስጋና አድርሰዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.