Fana: At a Speed of Life!

የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁ ትልቅ ስኬት ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም መከበሩን አስመልክቶ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልዕክት÷ እሴቱን ጠብቆ በኢትዮጵያውያን መካከል አብሮነትንና ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ደምቆ እንዲከበር ለረዳን ፈጣሪ ምስጋና እያቀረብኩ፣ በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ጉልህ ሚና ለተጫወቱት አካላት ሁሉ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል።

የኢሬቻ በዓል ሳይበረዝና ሳይደበዝዝ ወጉና እሴቱን ጠብቆ ከትውልድ- ትውልድ እንዲሸጋገር ላደረጋችሁ፣ ዛሬም በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር የአንበሳውን ድርሻ የተጫወታችሁ አባ ገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች ‘ገለቶማ’ ልላችሁ እወዳለሁ ነው ያሉት፡፡

የበዓሉ ድምቀት የሆናችሁ ቄሮና ቀሬዎች፣ በባህላዊና አልባሳት በመጌጥ የኢሬቻን ምንነት ከማስተዋወቅ በተጨማሪ፥ እርስ በረስ በመጠባበቅ የሰላም ዘብ በመሆን ላበረከታችሁት አስተዋፅኦ ምስጋናዬ የላቀ ነው ሲሉም አቶ ሽመልስ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ ቤት ያፈራውን ይዛችሁ በየአቅጣጫው ወንድሞቻችሁን በታላቅ ክብር ተቀብላችሁ በማስተናገድ ላሳያችሁት ታላቅ ፍቅር ምስጋናየን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ ብለዋል።

በተጨማሪም ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ዘብ በመቆም በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ላደረጉ የፈደራል፣ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጸጥታ አካላት አመስግነዋል፡፡

የኢሬቻ በዓል አከባበር መስህብ ይሆን ዘንድ የዓለም ማህበረሰብ እንዲያውቀው ላደረጋችሁ የሀገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ የሚዲያ ተቋማት በሙሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

በነገው እለት በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የሆረ ሀርሰዴ ኢሬቻ ልክ እንደ ሆረ ፊንፊኔው እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በድጋሚ መልካም የኢሬቻ በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ ሲሉም ገልጸዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.