Fana: At a Speed of Life!

የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም መከበሩን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የረራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በደመቀና ባማረ ሁኔታ የገዳ ስርአቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም መከበሩን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

ለበዓሉ በሠላም መከበር የድርሻቸውን ለተወጡ አካላት በሙሉ ግብረ ኃይሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

አባ ገዳዎች ፣ ሀደ ሲንቄዎች ፣የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ  ክፍሎች የመጡ  እንግዶች እንዲሁም የውጪ ሀገር ጎብኚዎች የታደሙበት የ2015 ሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም እና በልዩ ድምቀት መከበሩን  የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

የፀጥታ አካላት ለወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከልና ምርመራ ተግባራት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አባላትንና አመራሮችን በመመደብ እና በተለይም ህብረተሰቡን አጋዥ በማድረግ ባከናወኗቸው ተግባራት በዓሉን በሰላም ማክበር ተችሏልም ነው ያለው፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ፣ የበዓሉ አስተባባሪዎች ፣ በየእርከኑ የሚገኙ የአስተዳደር አካላት የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የመጡ እንግዶችን በወንድማማችነትና በእህታማማችነት መንፈስ ማስተናገዳቸውንም አንስቷል።

ከዚህ ባለፈም ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ለበዓሉ ሰላማዊነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው እንዲሁም መላው የፀጥታ አካላት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ኃላፊነታቸውን በብቃት በመወጣታቸው በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንደተከበረም ነው ያስታወቀው።

በዓሉ በሰላም መከበሩ የከተማዋን መልካም ገፅታ ለመገንባት  ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ያነሳው ግብረ ኃይሉ፥  በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር የድርሻቸውን ለተወጡ አካላት እንዲሁም ድካማቸውን ተቋቁመው ኃላፊነታቸውን በትጋት ለተወጡ መላው የፀጥታ አካላት አባላትና አመራሮች ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብር ኃይል  በድጋሚ መልካም ምኞቱን እየገለፀ  መስከረም 22 ቀን 2015 ዓ.ም በቢሾፍቱ የሚከበረው የሆረ ሀርሰዲ የኢሬቻ በዓል በተመሳሳይ በሰላም እንዲከበር ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.