Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ተወላጆች ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታ እንሰራለን አሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታ እንሰራለን ሲሉ ገለጹ።

“እየተከላከለች፥ እየለማች ያለች ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በሰሙት ንግግር፥ እንደሌሎች ኢትዮዽያውያን ወገኖች የትግራይ ህዝብና ተወላጆች ከለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥት የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አብራርተዋል።

አሻባሪው ህወሓት በሀገረችን ኢትዮጵያ ላይ ግልፅ የሆነ ጦርነት ካወጀበት ጊዜ አንስቶ ፖለቲካዊ፣ ማሀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በአገረቱ እንዲከሰቱ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ጦርነትና ጠብ አጫሪነት የተጠናወተው አሸባሪው የህወሓት ቡድን ፍላጎቱን መተግበር እንዳልቻለና ይልቁንም የትግራይን ህዝብ ለመከራ እየደረገው እንደሚገኝ ነው አቶ ኢብራሂም ያስረዱት።

በመድረኩ የተሳተፉት በድሬደዋ ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ከምንም በላይ ከመንግስተ ጎን በመሰለፍ ለሀገራቸው ሰላምና ፀጥታ እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።

አሸባሪው ቡድን እየፈፀመ ያለውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና የጀመረውን 3ኛ ዙር የጥፋት ጦርነት እንደሚያውግዙ ገልጸው፥ መንግስትም አሸበሪውን ቡድን በመደምሰስ የሀገርን ሠላም እንዲያረጋግጥ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የዓለም መንግስታትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የአሸባሪውን ቡድን ድርጊት በተለይም ሕጻናትን ለጦርነት እየማገደ መሆኑን አጥብቆ እንዲያወግዝም ነው የጠየቁት። የሀገር ሠላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ ድጋፉን ሊሰጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሁሉም ትግራዋይ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አሻባሪው የህወሓት ቡድን የሚያስተላልፋቸውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎች ወደ ጎን በመተው ለአገራቸውና ለህዝባቸው ሰላምና ፀጥታ እንደምቆሙም ጠቁመዋል።

በምንያህል መለሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.