Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የምታከናውነውን የአየር ንብረት ለውጥ ሥራ እንደሚደግፍ የተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የምታከናውነውን የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራ እንደሚደግፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም አስታወቀ፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ የፕሮግራሙን የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ማርጋሬት አዱክን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይቱ ሚኒስትሯ የአሥር ዓመቱን የልማት እቅድ በዝርዝር ያብራሩ ሲሆን÷ በተለይም መንግሥት ለአካባቢ ጥበቃ ሥራና ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የተሰጠውን ትኩረት ገልጸዋል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ፣ አረንጓዴ አሻራና ሌሎች በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ የተሰሩና በሥራ ላይ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ አብራርተዋል።

ይህንን ሀገራዊ ተግባር የመደገፍ ፍላጎት ያላቸውን አካላት መንግሥት ያበረታታልም ነው ያሉት።

የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ተወካይዋ ዶክተር ማርጋሬት ኦዱክ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና መቋቋም ረገድ እየሰራች ያለችውን ስራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና የሚሰጠውና የሚደግፈው ነው ብለዋል፡፡

እስካሁንም ቢሆን ፕሮግራሙ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጋራ ሲሰራ ቆይቷል ያሉት ተወካይዋ፥ በቀጣይም ይህንን አጠናክሮ መቀጠል ይፈልጋል ማለታቸውን ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.