Fana: At a Speed of Life!

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም እንዲካሄድ በቂ ዝግጅት አድርጌያለሁ አለ ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በመቀናጀት የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገለፀ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከትምህርት ሚኒስትርና ከክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ኮሚሽነሩም ፥ በፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራት ትውልድ የሚቀረጽበትን የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ እንደ አንድ ትልቅ ተልዕኮ ወስደን በኃላፊነት መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

አያይዘውም አሸባሪው የህወሓት ቡድን ላለፉት ዓመታት ሀገር እንዳይጠነክር፤ ትውልድ በሰላም እንዳይኖር እነርሱ ብቻ እንዲገዙና በደከመ ሀገር ውስጥ እንደፈለጉ መቆየት እንዲያስችላቸው ሆን ብለው የትምህርት ሥርዓቱን በማዳከም ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡

መንግስት የትምህርት ስርዓቱን ለመቀየር ከፍተኛ በጀት መድቦ ቀላል የማይባሉ ተግባራትን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

ፈተናው ከማንኛውም የፀጥታ ችግር ነፃ ሆኖ ተፈታኞች ያለምንም ስጋት ተረጋግተው መፈተን እንዲችሉ የፀጥታ መዋቅሩ ፈተናውን አጅቦ ለማጓጓዝና ጠንካራ ፍተሻዎችን ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ነው የተናገሩት፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ዲኤታ ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው ፥ ተማሪዎች ለፈተና ሲቀርቡ ስለት ያላቸውን ብረቶችንና ጠንካራ ፕላስቲኮች፣ አደንዛዥ ዕፅ፣ ጫት፣ ሲጋራ፣ የአልኮል መጠጥ ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም ክልክል ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሃኪም ማዘዣ የሌለው መድሃኒት በሽሮፕም ሆነ በታብሌት፣ የህክምና መስጫ መርፌ፣ የአንገት ሀብል፣ የጸጉር ጌጥ፤ የጆሮ ጌጥ፤ የጣት ቀለበት፤ የእጅ አንባር አድርጎ ወይም ይዞ መገኘት እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ስልክ፤ አይ-ፓድ፤ ታብሌት፤ ላፕቶፕ፤ ስማርት ሰዓት ፤ ማጂክ ብዕር (እስኪሪቢቶ)፤ ማጂክ ኮት(ጃኬት)፤ የግል ፍላሽ ዲስክ፤ ሲዲ፤ ሚሞሪ፤ ሚሞሪ ሪደር፤ ኦ-ተጂ ኮንቨርተርና ፎቶ የሚያነሱ እና ድምፅ የሚቀርፁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዞ መገኘት ለተፈታኞች የተከለከሉ ተግባራት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም እነዚህ የተከለከሉ መሳሪያዎችን በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥም ሆነ በዙሪያው ይዞ መገኘት፣ ፈተና ከተጀመረ ከ30 ደቂቃ በኋላ ወደ ፈተና ክፍል መግባትና ፈተናው ተጀምሮ 45 ደቂቃ ሳይሞላ ከፈተና ክፍል መውጣት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ጊቢ ወስጥ በግልም ሆነ በቡድን መጮህ ወይም በጣም ከፍተኛ ድምፅ ማሰማት የተከለከለ ነው ብለዋል፡፡

ይህን ተላልፎ የተገኘ ተማሪ ላይም ጥብቅ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ማሳሰባቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.