Fana: At a Speed of Life!

138 የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አመራሮችና አባላት ተማረኩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን የሽብርተኛው ሸኔ ቡድን የደቡብ ቀጠና ምክትል አዛዥን ጨምሮ 138 በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አመራሮችና አባላት ተማርከዋል።

 

ቡድኑ ለህዝብ ጥቅም እሰራለሁ ከሚለው የማደናገሪያ ሃሳቡ በተቃራኒ የቆመና የህዝቦችን ስቃይ የሚያረዝም ሽብርተኛ ሃይል እየሆነ መምጣቱ ወደ መበታተን ደረጃ እያደረሰው መሆኑን ምርኮኞቹ ተናግረዋል።

 

ከምርኮኞቹ አንዱ የሆነው እና የታጣቂ ሃይሉ የደቡብ ቀጠና ምክትል አዛዥ አቶ መሃመድ አሜ÷ ከአመታት በፊት በሃገራችን የተዘረጋውን የሰላም አማራጭ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደሀገር መግባቱንና ለሀገር የሚበጅ ተግባር ለመፈፀም ህልም እንደነበረው ተናግሯል።

 

ሆኖም ግን አሸባሪው ቡድን ከዚህ በተቃራኒና ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ህዝቦችን ለመከራ፣ ቀጠናውን ለሰላም እጦት መዳረጉን በሂደት በማስተዋሉ ትግሉን ለማቋረጥ መገደዱን ጨምሮ ገልጿል ሲል የዘገበው ኢቢሲ ነው።

 

ምርኮቹ፥ የሸኔ የሽብር ቡድን የምንታገለው ለኦሮሞ ህዝቦች ነፃነት ነው በሚል ወጣቱን ሃይል በማደናገር ብዙዎችን ያሳሳተ የእኩይ አላማ ስብስብ ነውም ነው ያሉት፡፡

 

አሁን መንግስትና የፀጥታ ተቋማት እየወሰዱት ያለው የተጠናከረ ዘመቻ ከሸኔ ውስጣዊ ችግሮች ጋር ተዳምሮ ቡድኑ የለየለት አቅም ማነስ ውስጥ እንደሚገኝ የሚናገሩት ምርኮኞቹ ÷ በአሸባሪ ቡድኑ ውስጥ ያሉ ወጣቶችም እጃቸውን ለፀጥታ ተቋማት በመስጠት ራሳቸውን እንዲያድኑ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የደቡብ ዕዝ የኋላ ደጀን አስተባባሪ ኮሎኔል ግርማ አየለ በበኩላቸው ÷የፀጥታ ግብረ ሃይሉ መላውን ህብረተሰብ በማሳተፍ እየወሰደው ባለው እርምጃ የሽብርተኛው የሸኔ ታጣቂ ቡድን አባላት በየዕለቱ እጃቸውን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.