Fana: At a Speed of Life!

በጥቅምት ወር የመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለግብርና ሥራ ምቹ ነው- ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጥቅምት ወር የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት በአብዛኛው በደቡብና በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የእርጥበት ገጽታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የመኸር ሰብል አምራች በሆኑትም ሆነ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች የእርጥበት ሁኔታው ከቀደመው አንጻር ሲታይ ከሞላ ጎደል ጥንካሬ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

ስለሆነም በምዕራባዊው አጋማሽና በደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ እርጥበት እንደሚኖራቸው ከመጠበቁ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ለሚያከናወኑ የግብርና ሥራዎች በጎ ጎን ይኖረዋል ነው ያለው ኢንስቲትዩቱ፡፡

ለመኸር ሰብል አብቃይ ቦታዎችና ዘግይተው ለተዘሩና ዕድገታቸውን ላልጨረሱ የመኸር ሰብሎች እንዲሁም ቋሚ ተክሎች የውኃ ፍላጎትን ለማሟላት ያግዛል ተብሏል፡፡

እንዲሁም እርጥበታማ የአየር ሁኔታው ወደ ደቡብ በሚያደርገው መስፋፋትበደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች ደጋማ አካባቢ ላይ የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል መባሉን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ በአካባቢው ለሚኖሩ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ሣርና ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት ጥሩ አስተዋጽዕ እንደሞኖረውም ነው የተጠቆመው፡፡

በሌላ በኩል ውኃ አጠር የሆኑ አካባቢዎች የሚገኘውን የዝናብ ውኃ ለማከማቸት መልካም አጋጣሚ ስለሚያገኙ ይህንኑ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ መክሯል፡፡

በመደበኛ ሁኔታ የሰብል በሚሰበሰብባቸው በሰሜናዊ አጋማሽም ሆነ በአንዳንድ ቆላማ አካባቢዎች ሊኖር የሚችለው ደረቅ ሁኔታ ለሰብል ስብሰባ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተጠቁሟል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.