Fana: At a Speed of Life!

ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ለባቡር መንገድ ሥራ የሚውሉ ዕቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ለባቡር መንገድ ሥራ የሚውሉ ዕቃዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አስታወቀ።

የሚመለከታቸው የክልልና የፌደራል መንግሥታት ንብረቶቹን በአግባቡ ሊያስጠብቁ ባለመቻላቸው በአካባቢው ለሚፈጠሩ ጸቦች ሰበብ እየሆነብኝ ነው ብሏል ፖሊስ፡፡

የአስተዳደሩ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር መስፍን ብርሃኑ እንደገለጹት÷ ከወልዲያ- ሀራ ገበያ -ኮምቦልቻ እየተዘረጋ የነበረው የባቡር መንገድ ሥራ በጦርነቱ ምክንያት ሥራው ቆሟል፡፡

ሥራውን በበላይነት ሲያከናውን የነበረው የቱርኩ ያፒ መርከዚ የባቡር ድርጅትን ጨምሮ ፕሮጀክቱን በላይነት የሚመሩ የፌደራል አካላት ንብረቱን በአግባቡ ባለመሰብሰባቸው ለዘረፋና ብክነት ተዳርጓል፡፡

በዘራፊዎች ሸዋሮቢትን አቋርጠው ሊወጡ ሲሉ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው÷ መዳቦች፣ የትላልቅ ተሽከርካሪ ሞተሮች ፣ የሀዲድ ብረቶች እንዲሁም ልዩልዩ ዕቃዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

ንብረቶቹ የሕዝብ በመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት ለመሰብሰብ ጥረት እያደረገ ቢሆንም÷ በአዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁም በግለሰቦች መካከል የጸብና የወንጀል መነሻ በመሆን ለከተማው ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ችግር እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም የሚመለከተታቸው የክልልና የፌደራል አካላት ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

በተደጋጋሚ ንብረቶቹ አላግባብ እየባከኑ መሆኑን ለሚመመለከታቸው አካላት ማሳወቃቸውንየሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.