ከስደት ተመላሽ ዜጎችን አሰልጥኖ ወደ ሥራ ለማሰማራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፈርስት ኮንሰልት ኢትዮጵያና ጃምቦ የፅዳት አገልግሎት ጋር በመተባበር 5 ሺህ ከስደት ተመላሾችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ÷ ከፈርስት ኮንሰልትና ጃምቦ ኢትዮጵያ ጋር የተደረገው የሦስትዮሽ ስምምነት የሴቶችና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስት እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
5 ሺህ ከስደት ተመላሾችን በፅዳት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ የሚጀመረው ሥራ በቀጣይም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን÷ ከሥደት ተመላሽ ዜጎችን ለማቋቋምና ወደ ሥራ ለማሰማራት በርካታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ግብረኃይል መቋቋሙን ገልፀዋል፡፡
የግብረ ኃይሉ አባል የሆነው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሥደት ተመላሾቹን የማሰልጠንና መንግስታዊ ድጋፎችን እንዲያገኙ የማመቻቸት ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ማስረዳታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የፈርስት ኮንሰልትና ጃምቦ የፅዳት አገልግሎት ተወካዮች በፊርማ ሥነ-ሥረዓቱ ወቅት ÷በፅዳት ሥራ መነሻ ክህሎት ይዘው ወደ ሃገራቸው የተመለሱ ወጣቶችን በተለይም ሴቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!