Fana: At a Speed of Life!

በዓላት በስኬት እንዲጠናቀቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 23 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሰሞኑ የተካሄዱትን ህዝባዊ በዓላት ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ እንዲከበሩ ከፍተኛ ሚና ላበረከቱት የፀጥታ አካላት፣ የሃይማኖት ተቋማትና አባ ገዳዎች እውቅና እና ምስጋና ሰጠ፡፡

በእውቅናና ምስጋና መርሐ ግብሩ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ በኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ወዳድነት የአደባባይ ህዝባዊ በዓላት በአስቸጋሪ ወቅት ላይ ሆነን ከምንም ጊዜ በላይ ውጤታማ በሆነ መልኩ ማክበር መቻሉን ገልፀዋል።

ህዝባዊ በዓላቱ ያለ ምንም ልዩነት የጋራ በዓሎቻችን ናቸው በማለት ሁሉም በያለበት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ የኢትዮጵያን ገፅታ ከፍ ባለ መልኩ ማክበር ችለናልም ነው ያሉት።

ከንቲባዋ ተቀራርበንና ተደጋግፈን በመስራትና በመተባበር በሌሎች ሥራዎቻችን ላይ ውጤታማ መሆን እንደምንችል የታየባቸው ህዝባዊ በዓላት እንደነበሩም አንስተዋል።

አሁን ላይ ህዝባዊ በዓላትን በአደባባይ ወጥቶ ለማክበር ምቹ ባልሆነበት ሁኔታ በሰላም ወዳዱ ኢትዮጵያውያን፣ በፀጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ አባገዳዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ቅንጅት በዓላቱ ስኬታማ ሆነው መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች በሁሉም ደረጃ ህዝባዊ በዓላቱ እጅግ ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቁ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.