Fana: At a Speed of Life!

የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ለመንከባከብ የተጀመረው ሕግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – የሐረሪ ክልል መንግሥት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የተጀመረው ሕግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የክልሉ መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ÷ በጀጎል ግንብ ውስጥ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች፣ አድባራት፣ መስጂዶች፣ ሙዚየሞች፣ ታሪካዊ፣ ሐይማኖታዊ እና ጥንታዊ ቅርሶች ከተደቀነባቸው አደጋ ለመታደግ በመንግሥት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ቅርሱን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የተጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ስለሚቀጥል የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመሆን ኃላፊነቱን እንዲወጣ የክልሉ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል፡፡

በጀጎል ግንብ ውስጥ እና ዙሪያው የሚታየው ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ የቤት ግንባታና እድሳት፣ የመሬት ውስጥ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ የመኪና እጥበት እንዲሁም ሌሎች ተግባራት ቅርሱን በስጋት ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች ናቸው ብሏል መግለጫው፡፡

ቅርሱን በተቀናጀ መልኩ ለመጠበቅና ለመንከባካብ የተቋቋመው ግብረኃይል ከተለያዩ ተቋማትና ከመላው ሕዝብ ጋር በመሆን አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በቅርሱ ላይ የተደቀኑ ችግሮችን ለመቅረፍ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማጎልበት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

ቅርሱን የመጠበቅ፣ የመንከባከብና ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት የሁሉም መሆኑንም የክልሉ መንግሥት ገልጿል፡፡

የሐረሪ ክልል ካቢኔ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ÷ በጀጎል ግንብ ውስጥና ዙሪያ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች እንዲጠናከሩ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.