Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ በዓየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ናት ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ በዓየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗንና ለዚህም አስቸኳይና ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ፡፡

ከ40 በላይ ሀገራት በግብፅ ህዳር ላይ ሊካሄድ ከታቀደው የኮፕ27 ስብሰባ በፊት የጋራ አቋም ለመያዝ በኮንጎ ኪንሻሳ ምክክር አድርገዋል፡፡

በምክክሩም የኮንጎው ጠቅላይ ሚኒስትር ዣን ሚሼል ሳማ ሉኮንዴ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ያለውን የዓለም የሙቀት መጠን ለመቀነስ እንዲሁም የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመግታት የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኮንጎ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ኤቭ ባዛይባ ማሱዲ በበኩላቸው ፥ አፍሪካ በዓየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላት ተፅዕኖ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ውይይቶቹ ለዚህ ችግር በዋነኛነት ድርሻ ያላቸው ሀገራትን የሚያካትት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ቀደም ሲል እገዳ የጣሉባቸውን የኃይል ምንጮች በድጋሚ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

ይህም በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የሚደርሰውን የኃይል እጥረት ለመከላከል በማሰብ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

አሁን ላይ አፍሪካ አጣብቂኝ ውስጥ ትገኛለች ያሉት የኮንጎ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሩ ፥ አህጉሪቱ ለዓለም ሙቀት መጨመር የምታበረክተው 4 በመቶ ብቻ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡

ለዚህ ችግርም አስቸኳይና ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያሻው በመድረኩ መነሳቱን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ግብፅ የምታስተናግደው ቀጣዩ ጉባዔ ፥ ሀገራት የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመግታት የገቡትን ቃል አፈጻጸም በተመለከተ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.