Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ህዝብና መንግስት ለመከላከያ ሠራዊት ከ70 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ህዝብና መንግስት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ70 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አስረከበ።

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ እንዳሉት ፥ የደቡብ ክልል ለመከላከያ ሰራዊቱ የተሰበሰበዉ ድጋፍ ሰንባች ምግቦችና የቁም እንስሳትን ጨምሮ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል፡፡

በዚህም በአጠቃላይ ከ70 ሚሊየን 551 ሺህ ብር በላይ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።

ወ/ሮ ፋጤ አክለውም ፥ አሸባሪው ህወሓት የብልጽግና ጉዞውን ለማሰናከልና የሀገርን ሰላም ለማደፍረስ ጥረት እያደረገ የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡

የአሸባሪውን ዓላማ ለማምከንም የክልሉ ህዝብ ልጆቹን ግንባር ድረስ ከመላክ ባሻገር ገንዘቡን፣ ምርቱንና ሰንጋውን ጭምር እያበረከተ ይገኛልም ነው ያሉት።

ይህ ሁለንተናዊ ድጋፍና የነቃ ተሳትፎ ወራሪው ሀይልም ሆነ እሱ የጋበዛቸው የውጭ ሀይሎች ስጋት እስኪወገድና ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው ፥ የኢትዮጵያ ህዝብ በሁሉም ግንባር ተሰልፎ ለመከላከያ ሠራዊት ጠንካራ ደጀንነቱን እያሳየ በመሆኑ አመስግነዋል፡፡

በሁሉም ዘርፍ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.