Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ በ2014 ዓ.ም በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ተነገረ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2014 ዓ.ም በመንገድ ደኅንነት ችግር ሕይወታቸውን የተነጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ2013 አንጻር በ11 ነጥብ 4 በመቶ መቀነሱን የአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት አስታወቀ።

በ2013 ዓ.ም የነበረው የትራፊክ አደጋ ሞት ቁጥር ምጣኔ በ100 ሺህ 11 ነጥብ 6 በመቶ እንደነበርም ተነግሯል፡፡

በተጠቀሰው ዓመት በትራፊክ አደጋ በ411 ሰዎች የሞት እና በ1 ሺህ 900 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ባሳለፍነው ዓመት ለዕይታ ጨለማ የሆኑ መንገዶችን በመለየት የመብራት አምፓል የመትከል ፣ የመንገድ ጥገና የማድረግና የተሽከርካሪ ቁጥጥር በማድረግ አስከፊውን የትራፊክ አደጋ የመቀነስ በርካታ ተግባራትን ሲከወን መቆየቱም ነው የተነገረው።

የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ኃላፊና የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ምትኩ አስማረ፥ ምክር ቤቱ የጀመራቸውን ስራዎች በማጠናከር የተመዘገቡ ውጤቶችን እንደመነሻ በመውሰድ ለላቀ ውጤት መስራት እንድሚገባም አስገንዝበዋል።

በበዓል ወቅት በአስፓልት መንገድ ላይ የሚደረግን ግብይት ለማስቀረት ለከተማው ማኅበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መሰጠት እዳለበትም የአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት አሳስቧል።

የህዝብ ቁጥር መጨመር እና በመንገድ ዳር የሚከወን የማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መጨመር ለትራፊክ አደጋው መንስዔ ሆነው መቆየታቸውን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.