ጤና

የጨጓራ አሲድ ወደ ጉሮሮ መመለስ እንዴት ይታከማል?

By Shambel Mihret

October 04, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጨጓራ አሲድ ወደ ጉሮሮ ሲመለስ በሰዎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ከአንገት በላይ ሀኪም ዶክተር ደሳለኝ ጥላሁን÷ ምግብ፣ አሲድና ምግብ እንዲደቅ የሚያደርጉ ኢንዛይሞች ከጨጓራ ወደ ጉሮሮ ሊመለሱ እንደሚችሉና እነዚህም በሰዎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ ገልጸዋል፡፡

ከጨጓራ ወደ ላይ ወይም የምግብ ቧንቧ ወደ ሚባለው ክፍል (Esophagus)፣ ወደ ጉሮሮ ክፍልና የመተንፈሻ ቱቦ ላይ ሊመለሱ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ አሲዶችና ኢንዛይሞች ሲመለሱ በሰዎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉም ነው ያሉት የህክምና ባለሙያው፡፡

ከጨጓራ ወደ ጉሮሮ መተላለፊያ ላይ መቆጣጠሪያ መኖሩን የተናገሩት ዶክተር ደሳለኝ  የእሱ  መላላት በቀላሉ ከጨጓራ ወደ ላይ ምግብ፣ አሲድና ኢንዛይሞች እንዲያልፉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ጉሮሮ ላይ የተለጠፈ ወይም ባዕድ ነገር ያለ የሚመስል ስሜት መሰማትና በተደጋጋሚ ጉሮሮን ማጽዳት የጨጓራ አሲድ ወደ ጉሮሮ መመለስ የመጀመሪያ ምልክቶች ናቸውም ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም የምራቅ ወይም አክታ መወፈር ምልክት ሊኖር እንደሚችል ጠቅሰው÷ እያደገ ሲሄድ ደግሞ የድምጽ መጎርነን እና የአየር ማጠር ምልክትና በተደጋጋሚ ሳል ሊኖር ይችላል ብለዋል፡፡

የጨጓራ አሲድ ወደ ጉሮሮ መመለስ ምልክት ከመጀመሪያ ጀምሮ እየጨመረ እንደሚሄድና በጣም አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችልም  አመላክተዋል፡፡

ሰዎች ከጨጓራ ወደ ጉሮሮ መተላለፊያ ላይ ያለውን  የመቆጣጠሪያ ክፍል ሊያላሉ የሚችሉ ነገሮችን ሲጠቀሙ ለምሳሌ ሲጋራ ማጨስ፣ ቸኮሌት በተደጋጋሚ  መጠቀም ለበሽታው ሊጋለጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ለጉሮሮና ለጨጓራ ተስማሚ ያልሆኑ ነገሮችን አልኮልና በርበሬ የበዛባቸው ነገሮችን የሚጠቀሙ ሰዎች ህመሙ የበለጠ እየተባባሰባቸው እንደሚሄድም ተናግረዋል፡፡

ጉሮሮ አካባቢ ያለውን ባዕድ ነገር ያለ የሚመስል ስሜት ለማስወገድ ደግሞ በደጋጋሚ ጉሮሮን ማጽዳት ይኖራል ያሉት ዶክተር ደሳለኝ ጥላሁን÷ጉሮሯችን ስናጸዳ ይፋተጋል፤ በተቻለ መጠን እሱን  መቀነስ ይመከራል ብለዋል፡፡

ታማሚዎች ውሀን  በፊት ከሚጠጡት በበለጠ መጠጣት እንዳለባቸው ጠቅሰው÷ ጉሮሯቸውን ጥዋትና ማታ ጨው በተጨመረበት ለብ ባለ ውሃ ማጠብ እንደሚመከር ተናግረዋል፡፡

ለመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና÷ ከጨጓራ ተነስቶ ወደ ጉሮሮ የሚመለስ ጉዳት የሚያደርስ አሲድ መኖሩን አስታውሰው የህክምናው ዋና አላማም ይሄንን አሲድ መቀነስ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሲዱን ለመቀነስም የሚወሰዱ መድሐኒቶች መኖራቸውን ጠቅሰው÷ ሕክምናው ሊቆይ እንደሚችልና እስከ ሶስት ወር ድረስም መድሐኒት ሊሰጥ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ለውጥ ከሌለው ሌሎች የቀዶ ሕክምና አማራጮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ታማሚዎችም ከመተኛታቸው በፊት ሶስት ሰዓት ቀደም ብለው መመገብ ፣ማታ በጣም ጠግቦ አለመመገብና ሲተኙም ትራስ  መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል፡፡

እነዚህም ተግባራት የጨጓራ አሲድ  ወደ ጉሮሮ  እንዳይመለስ እንደሚረዱ ነው የህክምና ባለሙያው የተናገሩት፡፡

በሻምበል ምህረት