አንጌላ ሜርክል የተመድን የ2022 የናንሰን የሥደተኞች ሽልማት አሸነፉ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጀርመን የቀድሞዋ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በሶሪያ በተቀሰቀሰው ግጭት ለተፈናቀሉ ሶሪያውያን ከለላ በመስጠት ላበረከቱት በጎ አስተዋጽዖ የተመድን የሥደተኞች ሽልማት ማሸነፋቸው ተሰማ፡፡
የናንሰን ሽልማት ስያሜውንያገኘው በኖርዌያዊው አሳሽ፣ ተመራማሪ፣ ዲፕሎማት እና ሰብዓዊ ተግባር ላይ በተሰማራው ፍሪጆፍ ናንሰን ነው።
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ÷ በሶሪያ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ1 ሚሊየን በላይ ሥደተኞች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ አንጌላ ሜርክል ባሳዩት ታላቅ የሞራል ልዕልና እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የሰዎችን ሕይወት መታደግ በመቻላቸው እና ተመልሰው እንዲቋቋሙ በመርዳታቸው ለሽልማቱ መታጨታቸው ተመላክቷል፡፡
አንጌላ ሜርክል ሽልማቱን በፈረንጆቹ ጥቅምት 10 ቀን ጄኔቫ ላይ ተገኝተው ከሌሎች ዘርፎች አሸናፊዎች ጋር በሚኖረው መርሐ-ግብር ላይ እንደሚቀበሉ ተጠቁሟል፡፡
ከ150 ሺህ ዶላር ጋር የሚበረከተው የናንሰን ሽልማት ÷ ለድንበር አቋራጭ ሥደተኞች እና ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከለላ በመስጠት መድኅን በመሆን የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ግለሰቦች ፣ ቡድን ወይም ድርጅት የሚሰጥ ነው፡፡
አንጌላ ሜርክል በፈረንጆቹ 2015 እና 2016 ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሶሪያዊ ሥደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብለው ማስተናገዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መግለጹን አናዶሉ ዘግቧል፡፡