Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል በቴክኖሎጂ የታገዙ የግብርና ስራዎችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በቴክኖሎጂ የታገዙ የግብርና ስራዎችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳን ጨምሮ የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በጉራጌ ዞን በሶዶ ወረዳ በክላስተር የለማ የስንዴ ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

በመስክ ምልከታው ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ርስቱ፥ ከስንዴ ልማት በተጨማሪ የጤፍ ምርትንም በክላስተር የማምረት ልምድ ያለው አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“በኩታ ገጠምና በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ የሚሰራ የግብርና ማልማት ስራ ውጤታማ መሆኑንም ተመልክተናል” ብለዋል፡፡

የግብዓት አቅርቦትን በተመለከተ የመደገፍ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፥  የኮምባይነርና የትራክተር አቅርቦት ጥያቄዎችን መፍትሄ ለመስጠት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ከወር በኋላ ምርቱ እንደሚሰበሰብ የገለፁት የአካባቢው አርሶ አደሮች፥ ከግብርና  ባለሞያዎች ድጋፍ ሲደረግላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ስንዴን የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ለውጪ የማቅረብ አቅም እንዳላቸው ጠቅሰው፥ የሚደረግላቸው ድጋፍ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡

በወረዳው የስንዴ፣  የጤፍና ሌሎች ሰብሎችን በክላስተር  በማልማት ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በቀጣይም የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ  አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው፥ ከተሰራ ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት እንደሚቻል በመግለፅ  በቴክኖሎጂ የታገዙ የግብርና ስራዎችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በብርሃኑ በጋሻው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.