Fana: At a Speed of Life!

በጤናው ዘርፍ መረጃን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎችን በመስጠት ጥራት ያለው አገልግሎትን ለመስጠት ሰፊ ስራ ተሰርቷል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ መረጃን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎችን በመስጠት ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፊ መሰራቱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ተናገሩ፡፡

“መረጃን መሰረት ያደረገ ፍትኃዊ፣ ጥራት ያለው እና የማይበገር የጤና ስርዓት ማጠናከር” በሚል መሪ ቃል በቢሾፍቱ ከተማ ሀገር አቀፍ የጤና ስርዓት ጥናት ዓመታዊ ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፣ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራሮች፣ የምርምር ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ጨምሮ የተለያዩ አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል።

ሚኒስትር ዴዔታው በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ የተቀናጀ የጤና ስርዓት በጤና ኤክስቴንሽን ተግባራዊ በመደረጉ የመጀመሪያ የጤና አገልግሎት ማስፋፋት የተቻለ መሆኑንና በጤናው ዘርፍ ኢ-ፍትሃዊነትን ለመቀነስም ጉልህ ሚና እንደተጫወተም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው፥ ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰቡን ጤናና ስነ ምግብ አስመልክቶ የሚደረጉ ውሳኔዎችን የሚያግዙ ሳይንሳዊ መረጃዎች ለማቅረብ በርካታ ጥናቶችን እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የጤና ሚኒስቴር ጤናማ፣ አምራች እና የበለፀገ ህብረተሰብ ለማፍራት አልሞ የጤና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ያለውን ሥራ የሚያግዙ ከ100 በላይ የሚሆኑ ጥናት እና ምርምሮችን እያደረጉ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በመድረኩ ላይ የተለያዩ የጤና ስርዓትን መሠረት ያደረጉ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን ፥ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።

መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.