ጎፋ ገብርኤል አካባቢ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወደመ
አዲስ አበባ ፣መጋቢት 11፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ጎፋ ገብርኤል አካባቢ በደረሰ የእሳት አደጋ ሁለት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በአዲስ አበባ ወረዳ 6 በተለምዶ ጎፋ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ጋራዥ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ሁለት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጉዳት ሲደርስባቸው፥ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ደግሞ ወድሟል።
የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ፥ የእሳት አደጋው የደረሰው ትናንት ምሽት 2 ሰዓት ከ50 አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።
የእሳት አደጋው በአንድ ጋራዥ ላይ የደረሰ ሲሆን እሳቱን ለማጥፋት ከተሰማሩት 71 የእሳት አደጋ ሰራተኞች መካከል ሁለቱ ቀላል ጉዳት አጋጥሟቸዋል ነው ያሉት ሀላፊው።
ከዚህ ባለፈም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም ከ30 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከቃጠሎው ማትረፍ መቻሉንም ተናግረዋል።
እሳቱን ለመቆጣጠር አምስት ሰአታትን የፈጀ የማጥፋት ስራ የተከናወነ ሲሆን 250 ሺህ ሊትር ውሃ ጥቅም ላይ ውሏል።
የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
የእሳት አደጋውን በመቆጣጠር ሂደት የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።