Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ አህጉር አንድነት እንዲጠናከር ኢትዮጵያ በቀዳሚነት እየተጫወተች ያለውን ሃላፊነት ታስቀጥላለች – ቢቂላ ሁሪሳ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ አህጉር አንድነት እንዲጠናከር ኢትዮጵያ በቀዳሚነት እየተጫወተች ያለውን ሚና እንደምታስቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ ተናገሩ።
 
አዲስ አበባ በሚገኘው የቡሩንዲ ኤምባሲ አዘጋጅነት በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ወንድማማችነት ይበልጥ ለማጎልበት ያለመ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
 
በመርሐ ግብሩ የተገኙት ዶክተር ቢቂላ በኢትዮጵያ እና ቡሩንዲ መካከል ያለውን የረጅም ዘመን ግንኘነት አስታውሰው÷ሀገራቱ በቀጣይ በተለያዩ መስኮች በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ በሰላም ግንባታ ጥረት የምታደርገውን ጥረት አሁንም አጠናክራ እንደምትቀጥልም ነው ያረጋገጡት፡፡
 
በተለይም የአፍሪካ አንድነት እና የእርስ በርስ ግንኙነቱ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እንደምትጫወትም ዶክተር ቢቂላ አስገንዝበዋ።
 
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዬች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል በበኩላቸው÷ አፍሪካዊ ትስስርን ለማጠናከር በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ነፃነትን ለማቀናጀት የአፍሪካ ሀገራትን አጋርነት ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
 
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጭነት እየተከናወነ ያለው የወደፊት የአፍሪካ ወጣቶች የመሪነት ሚና ለማጎልበት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመላ አፍሪካ እንዲስፋፋም የወንድማማችነት ሁነቱ ትልቅ መሰረት የሚያስቀምጥ መሆኑንም አንስተዋል።
 
በኢትዮጵያ የቡሩንዲ አምባሳደር ዊሊ ኛሚቱዊ ÷ፓን አፍሪካኒዝም የጋራ ልማት እና ትብብር በማድረግ ለአፍሪካ ህልሞች በትብብር መስራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
 
ሀገራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረው አፍሪካን የማጠናከር እና የማቀራረብ ስራ በእጅጉ የምትደግፈው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
 
ሁለቱ ሀገራት በልዩ ልዩ ዘርፎች ያላቸውን ግንኘነት በማጠናከር ለዘላቂ ግቦች እንደሚሰሩ አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡
 
በመርሐ ግብሩ አምባሳደሮች ፣ ዲፕሎማቶች ከአፍሪካ ህብረት ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.