Fana: At a Speed of Life!

በቱርክ “አጊያን” ነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቱርክ ኢዝሚር ከተማ በሚገኘው “አጊያን” ነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚመራውና በቱርክ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው ልዑካን ቡድን በታሪካዊቷ እና በቱርክ የንግድ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በምታደርገው ኢዝሚር ከተማ በሚገኘው “አጊያን” ነጻ የንግድ ቀጠና ጉብኝት አድርጓል፡፡

ልዑካኑ በጉብኝቱ በነጻ ንግድ ቀጠናው የሚገኙ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች የስራ እንቅስቃሴ ላይ ምልከታ አድርጓል፡፡

የነጻ ንግድ ቀጠናው ዋና ዳይሬክተር እና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ሃላፊ ÷ ስለ ነጻ ንግድ ቀጠናው አመሰራረት እና አጠቃላይ አሰራር ለልዑካን ቡድኑ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አዲሱ ማሞ ÷ የኮርፖሬሽኑን አገልግሎት፣ ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮችን በተንቀሳቃሽ ምስል አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ ልዑኩ በነጻ ንግድ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙትን በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ ውጤቶች እና የከባድ መኪና ግብዓቶችን በሚያመርቱ ኩባንያዎች ጉብኝት አድርጓል፡፡

ከኩባንያዎቹ ባለቤቶች ጋር በኢትዮጵያ ባሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በቅርቡ በተቋቋመው የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ ሰፊ ውይይት መደረጉ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ “ሲሴክ” የተባለና ለአውሮፓ 25 በመቶ የምግብ ድርሻ የሚያቀርብ ኩባንያ ውስጥ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ ብሎም በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በግብርና ማቀነባበር ዘርፍ ስላለ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድል ገለጻ ተደርጓል።

ከጉምሩክ አሰራር ጋር ተያይዞ በነጻ ንግድ ቀጠናው ውስጥ ያለውን የተለየ አሰራር በ“አጊያን ” ከተማ የጉምሩክ ሃላፊ ሰፊ ገለጻ ተሰጥቶ ውይይት መደረጉን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይም ኮርፖሬሽኑ የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጠናን የማሳደግና ውጤታማ የማድረግ ሂደት ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱ ነው የተገለጸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.