ዓለምአቀፋዊ ዜና

በአሜሪካ በ“ኢያን አውሎ ንፋስ” ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 109 ደረሰ

By Alemayehu Geremew

October 05, 2022

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ከማክሰኞ ጀምሮ በ”ኢያን” አውሎ ንፋስ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 109 ደረሰ፡፡

ሕይወታቸውን ካጡት መካከል 105ቱ የፍሎሪዳ ነዋሪዎች መሆናቸውንም ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡

ከትናንት ምሽት ጀምሮ በመሬት መንሸራተት ምክንያት ከ400 ሺህ በላይ የፍሎሪዳ ነዋሪዎች የመብራት ኃይል እንደተቋረጠባቸው እና በጨለማ ውስጥ እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡

በመሬት መንሸራተቱ በርካቶች የፍሎሪዳ ነዋሪዎች ቤት አልባ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡

ትናንትና የፍሎሪዳ ገዢ የሆኑት ሮን ዴሳንቲስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፥ ወደ 79 ሺህ የሚጠጉ ሸጦች እንደተፈተሹ እና የነፍስ አድን ሥራዎች እንደተከናወኑ ታውቋል፡፡

አውሎ ነፋሱ ከ45 እስከ 55 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማስከተሉም ነው የተነገረው፡፡

የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ደግሞ በፍሎሪዳ የደረሰው የንብረት ውድመት መጠን 60 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል ብሏል።

በፈረንጆቹ መስከረም 28 የ“ኢያን አውሎ ነፋስ” በደቡብ ምዕራብ ፍሎሪዳ የመሬት መንሸራተት እንዲከሰት እና የሰዎችም ሕይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል፡፡