Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እርምጃ እየወሰደች ነው – አምባሳደር ተሥፋዬ ይልማ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ በዘላቂ ኢኮኖሚ ልማት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተሥፋዬ ይልማ ተናገሩ።

ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ እና ስደትን አስመልክቶ በተሰናዳው የካርቱም መድረክ መሪ ሐሳብ ውይይት ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ነድፋ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብሯም ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከሏን በተሞክሮነት አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በታዳሽ የኃይል ምንጮች እንዲሁም ከአነስተኛ እና ሰፋፊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የተገኘ የእህል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራትን በመለየት የኢትዮጵያን ልምድ አካፍለዋል።

የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ሕግ አውጪ ተቀዳሚ ምክትል አፈጉባዔ እና የወቅቱ የካርቱም የሥራ ሂደት ሊቀመንበር ሜሪ አየን ማጆክ ÷ የስደቶችን እንግልት ለመግታት በጋራ እናበቁርጠኝነት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

ስደተኞች አሰቃቂ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙባቸውም ሕጋዊ ጥበቃ ሊደረግላቸውና ሰብዓዊ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የካርቱሙ ሂደትም በአፍሪካ ቀንድ እና በአውሮፓ መካከል ባሉት የስደተኞች የጉዞ መስመር ላይ ባሉ ሀገራት መካከል የፖለቲካ ትብብር ለመመስረት የተካሄደ መድረክ ነው ተብሏል።

መድረኩ በስደት ላይ ቀጣይነት ያለው ውይይት እና ትብብር መመስረት የሚያስችል ምህዳር ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ዛሬ የተጀመረው ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ምሁራንን እያሳተፈ ያለው መድረክ ለሦስት ቀናት እንደሚቆይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.