አቶ ደመቀ መኮንን ለክትባቶች ተደራሽነት ከሚሰራው ዓለም አቀፉ የክትባቶች ጥምረት ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለክትባቶች ተደራሽነት የሚሰራው ዓለም አቀፉ የክትባቶች ጥምረት(ጋቪ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ሴዝ በርክሌይ ጋር ተወያዩ።
በዚህ ወቅት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2021 እስከ 2015 ሁሉንም ህጻናት የክትባት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችለውን ፕሮግራም እውን ለማድረግ ያላትን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ የህጻናትን ጤናማ ህይወት ለማረጋገጥ እና ፍትሃዊና ዘላቂነት ያለውን ክትባት ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ይረዳል ብለዋል።
ሴዝ በርክሌይ በበኩላቸው ከ20 አመታት በላይ የዘለቀውንና በኢትዮጵያ እና በጋቪ መካከል ያለውን ወዳጅነት አድንቀው፥ በሁለቱ ወገኖች በኩል የተያዘው አጀንዳ የመንግስት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በአፍሪካ ቀንድ ተላላፊ በሽታዎችን በመዋጋት እና የህጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ በኢትዮጵያ እና ጋቪ መካከል ያለውን አጋርነት አንስተዋል።
የህጻናት ክትባት ኢኒሼቲቭን በመተካት በፈረንጆቹ 2000 የተመሰረተው ዓለም አቀፉ የክትባቶች ጥምረት በታዳጊ ሀገራት ክትባትን ተደራሽ ለማድረግ የሚሰራ ጥምረት ነው።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!