Fana: At a Speed of Life!

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመር አይሲቲን የብልጽግና ጉዟችን ሞተር አድርገን የመንቀሳቀሳችን ማሳያ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመር ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን የብልጽግና ጉዟችን ሞተር አድርገን የመንቀሳቀሳችን ማሳያ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢንተርኔት አገልግሎት ማስጀመሪያ መረሐ ግብር በወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ነው፡፡
 
በመርሐ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ፣ የኩባንያው አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመር ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን የብልጽግና ጉዞአችን ሞተር አድርገን የመንቀሳቀሳችን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
 
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው፥ የሳፋሪ ኮም በኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመሩ ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ሳፋሪኮም ዛሬ በአዲስ አበባ እንዲሁም፥ባለፉት ሳምንታት በድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ አወዳይ፣ ጎንደር ፣ሞጆ፣ ሐረር፣ አዳማ፣ ሀረር፣ ቢሾፍቱና ደብረ ብርሃን ከተሞች የኔትዎርክ ሙከራ አገልግሎቱን ጀምሯል።
 
ኩባንያው (+2517) ኮድ ነው አገልግሎት መስጠት የጀመረው።
 
በአዲስ አበባ እና በአዳማ በ100 ሚሊየን ዶላር ወጪ የዳታ ማዕከል የገነባ ሲሆን፥በዚህ ዓመት በሁለቱም ከተሞች ሁለት ተጨማሪ የዳታ ማዕከል እንደሚገነቡ አስታውቋል።
 
በቀጣይ አሥር ዓመታት 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በማፍሰስም የዘርፉን ተጠቃሚነት የማሻሻል ዕቅድ እንዳለውም ነው ያመለከተው።
 
በብስራት መለሰ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.