የሰሜን ሸዋ ዞን እና ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር እና ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ድጋፉ ከዞኑ ነዋሪዎች፣ ከዞን፣ ከተማ እና ወረዳ አስተዳደሮች የተሰበበ ሲሆን÷ 59 የእርድ ሰንጋዎች፣ 981 በግና ፍየሎችን ጨምሮ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ያካተተ ነው፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ገንዘብ መምሪያ ኃላፊ እንግዳሸት በጋሻው ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደገለጹት÷ የሸዋ ሕዝብ የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ ለተሰለፈው መከላከያ ሠራዊት ደጀንነቱ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ጋሻው አስማሜ በበኩላቸው÷ በግንባር ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን በብልጽግና ፓርቲ የሰሜን ሸዋ ዞን ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም የጋምቤላ ክልል ለመከላከያ ሠራዊት 5 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ግምት ያለው 112 የእርድ ሰንጋዎች፣ በጎች እና ፍየሎችን ጨምሮ ሌሎች ምግብ ነክ ድጋፎችን አድርገዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃለፊ ኡቦንግ ኡቶው ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት÷ ከሕዝቡ እና አመራሩ የተሰበሰበውን 5 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አድርገናል፡፡
ድጋፉን የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ ተረክበዋል፡፡