Fana: At a Speed of Life!

ዓላማዬ መማርና ለሀገር በእውቀቴ ውለታ መዋል ነው- 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና  የሚወስዱት የ85 ዓመት አዛውንት

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 27 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለመውሰድ የመጀመሪያ ዙር ተፈታኞች ከትናንት  ጀምሮ ወደ ዩኒቨርስቲዎች እየገቡ ይገኛሉ።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲም  ከሀድያና ከወላይታ ዞኖች የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ የ12ኛ ተፈታኞች በመቀበል ላይ ነው።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ብሔራዊ ፈተናውን ከሚወስዱት ተፈታኞች መካከል ከወላይታ ዞን ባይራ ኮይሻ ወረዳ የመጡት የ85 ዓመቱ አቶ ባፋ ባጋጃ ይገኙበታል።

የስምንት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ባፋ ኑሮ ባደረሳባቸው ጫና እና ልጆቻውን አስተምረው ቁም ነገር ለማድረስ ሲሉ በ1949 ዓ.ም የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ትምህርታቸውን እንዳቋረጡ ይናገራሉ።

የ85 ዓመቱ አዛውንት በ2009 ዓ.ም ከ66 ዓመት በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት በድጋሚ በመጀመር በባይራ ኮይሻ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።

“እውቀት መቅሰም በእድሜ አይገደብም” የሚሉት አቶ ባፋ ያቋረጡትን ትምህርት ከአምስት ዓመት በፊት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የጀግንነት መገለጫ የሆነው የአደንና ፈረስ ግልቢያ ልምድ አለኝ የሚሉት አዛውንቱ ዓላማዬ ግን መማርና ለአገር በእውቀቴ ውለታ መዋል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በፈተና ወቅትም በግቢው የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማከናወን ዝግጁ ሆነን መጥተናል ያሉት አቶ ባፋ÷ ክልከላ የተደረገባቸውን ጉዳዮች በሚገባ መረዳታቸውን አመልክተዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.