የሀገር ውስጥ ዜና

የደቡብ ኮሪያው ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የልማት ትብብር ማጠናከር እንደሚፈልግ ገለጸ

By Alemayehu Geremew

October 07, 2022

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 27 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኮሪያው ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የልማት ትብብር ማጠናከር እንደሚፈልግ ገለጸ።

በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ከደቡብ ኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲፕሬዚዳንት ሂዩክ ሳንግ ሶህን ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ኤጀንሲው በሰው ኃይል ግንባታ፣ በገጠር ልማት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በአየር ንብረት ለውጥ ፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ በሠላም ግንባታ፣ በልማት እና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ በኢትዮጵያ ሊጫወት የሚችለውን ሚና አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደፊት በማምረቻው ዘርፍ የእሴት ሰንሰለት ላይ የያዘችውን በትብብር የመሥራት ፍላጎት በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።

በውይይታቸው ወቅት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የትምህርት ዕድል የሚያገኙበትን መንገድም ጠይቀዋል፡፡

የ“ኮይካ” ፕሬዚዳንት ሂዩክ ሳንግ ÷ ኤጀንሲው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

የ“ኮይካ” የትብብር መሥኮችም ኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥታ ከምትሠራባቸው ጉዳዮች ጋር ጎን ለጎን የሚሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በደቡብ ኮሪያ የትምህርት ዕድል የሚያገኙበትን ሁኔታም እንደሚያመቻቹ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።