የአልዛይመር ምልክቶች እና ህክምናው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አልዛይመር በአንጎል ውስጥ ያሉት የነርቭ ህዋሳት ወይም የነርቩ ሴሎች ሲሞቱ ወይም ሲዳከሙ የሚከሰት የነርቭ ህመም ነው፡፡
አልዛይመርን በተመለከተ ሃሳባቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያካፈሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ጤና ሃኪም እና መምህር ዶክተር ሰላም አበራ ÷በአንጎል ውስጥ ያሉት የነርቭ ህዋሳት ወይም የነርቩ ሴሎች ሲሞቱ ወይም ሲዳከሙ የተለያዩ የህመም ምልክቶች እንደሚያሳዩ ተናግረዋል፡፡
እንደተጎዳው የአንጎል ክፍልም የሚታዩት ምልክቶች እንደሚለያዩም ጠቁመዋል፡፡
ነገሮችን የመርሳት ወይም የመዘንጋት፣ ነገሮችን አቅዶ መስራት መቸገር፣ አካባቢን መቃኘትና መገንዘብ መቸገር ፣ በፅሁፍ ወይም በንግግር ሃሳብን በተፈለገው መልኩ መግለፅ አለመቻል፣ ሰው ሲያወራ ንግግሩን መገንዘብ አለመቻል፣ አዳዲስ የሆኑ የስሜት ለውጦች ለምሳሌ ድብርት የሚታዩ ምልክቶች መሆናቸውን ይናገራሉ።
በብዛት ደግሞ የተናገሩትን ነገር ደጋግሞ መናገር፣ በቅርብ ጊዜ የተከሰቱ ነገሮችን መዘንጋት፣ የያዟቸውን ቀጠሮዎች መርሳት፣ ቀኖችንና በፊት ይጠቀሟቸው የነበሩ እቃዎችን አጠቃቀማቸውን መዘንጋት ይገኝበታል፡፡
በጊዜ ከታወቀም መድሃኒት መውሰድ እንደሚገባ የሚገልጹት ዶክተር ሰላም፥ መድሃኒቶቹ የህመሙን ጉዞ እንዲገቱ ያግዛሉ፣ በተወሰነ መልኩም የህመሙን ምልክቶች እንዲቀንሱ በማድረግ ህመሙ የሚፈጥራቸውን ምልክቶች በመድሃኒት መቆጣጠር ይቻላል ነው ያሉት፡፡
የአልዛይመር ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚቻል የሚያነሱት ዶክተር ሰላም የልብ እና የደም ቧንቧ ችግሮች ሲኖሩ ለአልዛይመር የመዳረግ እድል ስለሚጨምር እነሱን መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ፣አመጋገብን ማስተካከል፣ ከሱስ እራስን ማራቅም ለህመሙ የመጋለጥ እድልን ለመቀነስ የሚረዱ ነገሮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው