Fana: At a Speed of Life!

1 ሺህ 497ኛው የመውሊድ በዓል በጀማ ንጉሥ መስጂድ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሺህ 497ኛው የመውሊድ በዓል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መውሊድ በተከበረበት ጀማ ንጉሥ መስጂድ እየተከበረ ነው፡፡

በ1456 ዓ.ም የተመሰረተው ጀማ ንጉሥ መስጂድ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመውሊድ በዓል የተከበረበት ቤተ እምነት ነው፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን በበዓሉ አከባበር ላይ እንደገለጹት÷ ሀገራችን በሁሉም መልኩ የተቀደሰች ምድር መሆኗን የእምነት ተቋሞቻችን ታሪክ ያስረዳል፡፡

በጀማ ንጉሥ መስጂድ የመውሊድ በዓልን ስናከብር÷ ሰውነት ከሐይማኖት በላይ መሆኑን ያየንበትና የጋራ ሀገርን በፍቅር መገንባት መቻልን ተምረናል ነው ያሉት፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን በርካታ የመስህብ ስፍራዎች ቢኖሩም እነርሱን አውቆ ታሪካቸውን በማስቀጠል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲሰጡ በማድረግ ረገድ ውስንነቶች መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ውስንነቶችን በመፍታት የጎብኚ መዳረሻ ቦታዎችን በማልማት ሕዝባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ እንሠራለን ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ መሥፍን መኮንን በበኩላቸው÷ እስልምናና መውሊድ ሲነሣ የጀማ ንጉሥ መሥጂድ መስራቹ ሀጅ ሰይድ ሙጃሂድን ማንሳት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

ወሎ የሐይማኖት ሊቃውንት መፍለቂያ በመሆኑ አብሮነቱ የጠነከረ ፍቅርና መተሳሰብ ያለበት ነው ብለዋል፡፡

ቦታውን የጎብኚ መዳረሻ ለማድረግ ሕዝበ ሙስሊሙ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.