የሀገር ውስጥ ዜና

የመውሊድን በዓል የዓለምን ታሪክና የሰው ልጆችን ሕይወት በመለወጥ ማክበር ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

By Mikias Ayele

October 08, 2022

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመውሊድን በዓል የዓለምን ታሪክና የሰው ልጆችን ሕይወት በመለወጥ ማክበር እንደሚገባ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም በነቢዩ መሐመድ(ሰዐወ) መወለድ  ዓለም  እጅግ ተጠቅማለች፤  የዓለምን ታሪክም ቀይረዋል ብለዋል።

እንዲሁም የሰው ልጆችን ሕይወት ለውጠዋል ነው ያሉት።

የመውሊድን በዓል የምናከብረው  የዓለምን ታሪክና የሰው ልጆችን ሕይወት በመለወጥ መሆን አለበትም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

በግብርና እና በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ እየሠራን ያለው ሥራ የሀገራችንን ታሪክና የሕዝባችንን ሕይወት የሚለውጥ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያን ከጦርነት በመገላገል ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ታሪክና ሕይወት ወደሚለውጡ ዕቅዶቻችን እንዞራለን ብለዋል።

የተጀመረው “የሌማት ትሩፋት” የቤተሰቦቻችንን ሥርዓተ ምግብ እንዲለውጥ ተግተን እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።