የሀገር ውስጥ ዜና

የነብዩ መሀመድ ልደትን ስናከብር አስተምህሮታቸውን በማስታወስ ሊሆን ይገባል – አቶ ቀጀላ መርዳሳ

By Mikias Ayele

October 08, 2022

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የነብዩ መሀመድ ልደትን ስናከብር አስተምህሮታቸውን በማስታወስ ሊሆን ይገባል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ተናገሩ፡፡

በዓሉ በሚከበርብት አንዋር መስጊድ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ሚኒስትሩ ነቢዩ መሀመድ አዛኝ፣ ሩህሩህ እና የሰው ልጆች በፍትሀዊነት እንዲኖሩ የታገሉ ናቸው ብለዋል፡፡

ነቢዩ ከሰው ልጆችም በላይ ለእንስሳትና ለእፅዋት ሳይቀር አዛኝ፣ ሚዛናዊ ፍርድ ሰጭ እና የሰው ልጆችን በደልን አጥብቀው የሚቃወሙ እንደነበሩ አንስተዋል፡፡

በዓሉ የሰው ልጆች የሚደገፉበት፣ አቅመ ደካሞች የሚጎበኙበት፣ የታመሙት የሚጠየቁበት፣ ፍቅርን እና መተሳሰብን የሚታይበት በዓል በመሆኑ በዓሉን በሰብዓዊ ጉዳዮች ማሳለፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የመውሊድ በዓል ብሄራዊ በዓል መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ሰብዓዊነትን ማዕከል ያደረጉ እሴቶቻችን እንዳይመክኑ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

በዓሉ የሰላም የፍቅር እንዲሆንም ሚኒስትሩ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡