Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ በወላይታ ዞን ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ19 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን በወላይታ ዞን በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች ማቋቋሚያ የሚሆን ከ19 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ድጋፉን የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ሶዶ ከተማ ተገኝተው ለወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ አስረክበዋል፡፡

አቶ ደበሌ÷ኮሚሽኑ ከአሁን በፊት በሶዶ ከተማ በእሳት አደጋ ንብረታቸው ለወደመባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ዛሬ የተደረገው ድጋፍም ከ19 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ አልባሳት፣ ምግብ ነክ ግብዓቶችን እና የንፅህና መጠበቂያ ዕቃዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽነር ደበሌ የተደረጉት ድጋፎች ለትክክለኛ ተጎጂዎች በወቅቱ እና በስርዓት መድረስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው÷ በዞኑ በጎርፍ ምክንያት የተፈናቀሉ ከ1 ሺህ በላይ አባወራዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ያደረገው ድጋፍም ተፈናቃዮችን ለማቋቋም እንደሚያግዝ እና የተደረጉት ድጋፎች በፍጥነት እና በትክክል እንዲደርሱ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

የዞኑ አደጋ ስጋትና ዝግጁነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘውዱ ሳሙኤል÷ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የፌደራል የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ÷ ጉምሩክ ኮሚሽን የህዝብን ችግር ተረድቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ምላሽ በመስጠቱ ምስጋና አቅርበዋል።

በማቱሣላ ማቴዎስ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.