Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ በፈተና ማዕከላት የተከለከሉ ነገሮችን ይዞ መገኘት ከሁሉም ፈተናዎች እንደሚያሰርዝ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች በፈተና ማዕከላት የተከለከሉ ነገሮችን ይዘው ከተገኙ ከሁሉም ፈተናዎች የሚሰረዙ መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ ማምሻውን ባስተላለፈው መልዕክት ÷ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ወደ መፈተኛ ማዕከላት መግባታቸውን አንስቷል፡፡

የተከለከሉ ነገሮችን ማንም ተፈታኝ ይዞ እንዳይገባ ከወረዳ ጀምሮ ገለጻ ተደርጓል ያለው አገልግሎቱ ÷ በተጨማሪም አካላዊ ፍተሻ መደረጉን ጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ የተለያየ የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም የተከለከሉ ነገሮችን በተለይም ተንቀሳቃሽ ስልክን ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ይዘው የተገኙ ተፈታኞች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመላክቷል፡፡

ድርጊቱ ከፍተኛ የፈተና ደንብ ጥሰት መሆኑን የጠቆመው አገልግሎቱ ÷ በውሳኔውም ተማሪዎቹ ከሁሉም ፈተና የሚሰረዙ ይሆናል ነው ያለው ፡፡

በተመሳሳይ ከዚህ በኃላም የተከለከሉ ነገሮችን መፈተኛ ማዕከላት (የኒቨርሲቲዎች) ግቢ ውስጥ ማንኛውም ተፈታኝ ይዞ ቢገኝ ከሁሉም ፈተና የሚሰረዝ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ገለጻውን ባለመቀበልና አካላዊ ፍተሻዎችን በማጭበርበር ስለጸፈጸመው ጉዳይ ተጨማሪ ህጋዊ ምርመራ የሚካሄድ ሲሆን÷ እንደግኝቱም ተመጣጣኝ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ መገለጹን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

ፈተና የሁሉም ማህበረሰብ ኃብት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለፈተናው ደህንነትና ፍትሃዊነት የበኩሉን አዎንታዊ ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ለሚወስዱ ተፈታኞች የተከለከሉ ነገሮች ለማየት ሊንኩን ይጫኑ፡-

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ለሚወስዱ ተፈታኞች የተከለከሉ ነገሮች

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.