Fana: At a Speed of Life!

በህዳሴ ግድብ፣ አረንጓዴ አሻራ እና የስንዴ ምርት ያየነውን ውጤት በትምህርት ጥራት እንደግመዋለን – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዳሴ ግድብ፣ አረንጓዴ አሻራ እና የስንዴ ምርት ያየነውን ውጤት በትምህርት ጥራት እንደግመዋለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመላው አገሪቱ ለሚገኙ የ12ኛ ክፍል ፈታኝ መምህራን በበየነ መረብ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው፥ የፈተና ስርዓቱ በባለፉት አመታት ባልተገባ ሁኔታ የተለያየ ፍላጎት ባላቸው አካላት ለችግር የተጋለጠ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ዘንድሮ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ በተደረገው ጥረት የመምህራን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሃላፊነታቸውን በታማኝነት እንዲወጡ አደራ ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፥ እስካሁን በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ የነበረው ዝግጅት የተሳካ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተጀመረው መንገድ ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅም ፈታኝ መምህራንን ጨምሮ በሂደቱ ድርሻ ያላቸው አካላት በመተባበርና በሃላፊነት እንዲሰሩ አሳስበዋል ።

በሁሉም 12ኛ ክፍል ፈታኝ ዩኒቨርስቲዎች ለፈታኞች ገለጻ እየተደረገ ሲሆን፥ ከሰዓት በኋላ የተፈታኞች ገለጻ እንደሚደረግ ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.