Fana: At a Speed of Life!

ለፈተና ሄደው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለወለዱ ተፈታኞች በቀጣይ እንደመደበኛ ተማሪ እንዲፈተኑ ዕድል ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለፈተና ሄደው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለወለዱ ተፈታኞች በቀጣይ እንደመደበኛ ተማሪ እንዲፈተኑ ዕድል የተሰጣቸው መሆኑን የትህምርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ማምሻውን እንዳስታወቀው፥ በእርግዝና ላይ ላሉ እና ወልደው ጡት እያጠቡ ላሉ ለተመዘገቡ ሴት የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የእነርሱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የመፈተኛ ስርዓት በቀጣይ ተዘጋጅቷል፡፡

በመሆኑም ከመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሚሰጠው ፈተና መፈተን አያስፈልጋቸውም ብሏል፡፡

ይህም ከወራት በፊት ከወረዳ ደረጃ አንስቶ ገለጻ ተሰጥቷል፤ መመሪያ ሆኖ ወርዷልም ነው ያለው።

ሆኖም ለመፈተን ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመጡ ተፈታኞች መካከል ወደ ተቋማቱ እንደደረሱ የወለዱ እንዳሉ ሪፖርት እንደደረሰው አመልክቷል፡፡

ስለሆነም እነዚህ ወላድ ተፈታኞች የቤተሰብ ክብካቤና ፈተናውን ለመፈተንም አካላዊ ማገገሚያ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል።

በመሆኑም በቀጣይ እንደመደበኛ ተማሪ እንዲፈተኑ አገልግሎቱ ዕድል የሰጣቸው መሆኑን አስታውቋል።

ይህ ታውቆ ቀድሞ በተላለፈው መመሪያ መሠረት በመጀመሪያው ዙር መፈተን የማይችሉ መሆኑን ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.