Fana: At a Speed of Life!

የሰዋሰው መተግበሪያ ወደ ስራ መግባት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እቅድ የሚደግፍ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ”ሰዋሰው” መተግበሪያ ወደ ስራ መግባት ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታና የግሉ ዘርፍ ተዋናይ እንዲሆን የተያዘውን እቅድ የሚደግፍ ነው ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ ገለጹ፡፡

የጥበብ ስራዎችን በክፍያ እና በማስታወቂያ አማራጮች መከታተል የሚያስችል “ሰዋሰው” የተሰኘ መተግበሪያ ተመርቆ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

መተግበሪያው የጥበብ አፍቃሪያን የጥበብ ስራዎችን ካለ ክፍያ ከማስታወቂያ ጋር እና በክፍያ ካለ ማስታወቂያ መከታተል የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።

የስነ ጥበብ ሰዎች ከቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች ጋር በተያያዘ የሚገጥማቸውን ችግር የሚቀርፍ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷የሰዋሰው መተግበሪያው ወደ ስራ መግባት ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታና የግሉ ዘርፍ ተዋናይ እንዲሆን የተያዘውን እቅድ የሚደግፍ ነው ብለዋል፡፡

የክፍያ ስርዓቱ ከቴሌ ብር እና እናት ባንክ ጋር መተሳሰሩን አድንቀው÷ መተግበሪያው ዓለም አቀፍ መሆኑ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው÷ ከፍተኛ የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የተለየው አይ ሲ ቲ እና የጥበብ ዘርፍ ተቀናጅቶ ወደ ስራ መግባቱ የስራ እድል ፈጠራ ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በራይድ ቴክኖሎጂ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ለ46 ሺህ ሰው የስራ እድል ፈጥረናል ያሉት የራይድ ቴክኖሎጂ ባለቤትና የሰዋሰው ቦርድ ሊቀመንበር ወይዘሮ ሳምራዊት ፍቅሩ÷ ፈጠራ መር ኢኮኖሚን ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የጥበብ ሰዎች ከስራዎቻቸው የሚገባቸውን እንዲያገኙ በማድረግ ዘርፉ እንዲነቃቃ ያደርጋል መባሉን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.