በክሬሚያ ድልድይ ጥቃት የዩክሬን የደኅንነት አገልግሎት እጅ አለበት – ቭላድሚር ፑቲን
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከክሬሚያ ድልድይ ጥቃት ጀርባ የዩክሬን የደኅንነት አገልግሎት እጅ እንዳለበት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን መረጃውን ይፋ ያደረጉት የሩሲያ ወንጀል ምርመራ ኮሚቴ ኃላፊ አሌክሳንደር ባስትሪኪን ስለጥቃቱ ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ መሆኑን አር ቲ ዘግቧል፡፡
እንደ አሌክሳንደር ሪፖርት ከሆነ የተፈጸመው ጥቃት በዩክሬን የደኅንነት አገልግሎት የተቀነባበረ ሲሆን የሩሲያ እና የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ድጋፍ በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡
የምርመራ ኮሚቴው ከፍንዳታው ጋር በተገናኘ ተጠርጣሪዎችን መያዙንም ነው ያስታወቀው፡፡
የምርመራ ኮሚቴው ኃላፊ ድልድዩ ላይ ፍንዳታ የደረሰበት የጭነት ተሽከርካሪ ከቡልጋሪያ ተነስቶ ጆርጂያ እና አርሜኒያን አቋርጦ ሩሲያ እንደደረሰም አመላክተዋል፡፡
የተፈጸመውን ጥቃትም የሽብር ጥቃት ሲሉ ነው የፈረጁት፡፡
የክሬሚያ ድልድይ በሌላ ስሙ “የኬርች ድልድይ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በአውሮፓ ረጅሙ በባሕር ላይ የተገነባ መንታ መንገዶች ያሉት ድልድይ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
19 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ድልድይ በፈረንጆቹ 2014 ላይ በሩሲያ እንደተገነባና 3 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደተደረገበትም ነው የተነገረው፡፡