Fana: At a Speed of Life!

የህዝብ ብዛትን መሰረት በማድረግ ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት ይሰራል -ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እያደገ የመጣውን የህዝብ ብዛት መሰረት በማድረግ መንግስት ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ስርዓት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ተካሂዷል።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ፕሬዚዳንቷ የመንግስት ዕቅድን በሚመለከት ለሁለቱ ምክር ቤቶች ንግግር አድርገዋል።

ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት ፥ ያገባደድነው 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ በበጎም ይሁን በመጥፎ ብዙ ሁነቶችን ያስተናገደችበት ዓመት ነው፡፡

በዓመቱ ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸሞች እንደሚያሳዩት በ2014 ዓ.ም ሰፋፊ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች በኢኮኖሚው ላይ ያሳደሩት ጫና እንዳለ ሆኖ በጫናዎቹ ውስጥ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ስኬት ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ጥሎት ባለፈው ጠባሳ፣ ጦርነት በፈጠረው የኢኮኖሚ ውድመት እንዲሁም ጎርፍና ድርቅ ባሳደሩት አሉታዊ ተጽዕኖ ኢኮኖሚው ሳያሽቆለቁል ይልቁንም እድገት ማስመዝገብ መቻሉ ትልቅ ውጤት እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡

በወጪ ንግድ ዘርፍ የተገኘው ገቢ በወጪ ንግድ ታሪክ ከፍተኛ ሆኖ መመዝገቡን አንስተው ፥ ለዕድገቱ የወጪ ንግድ ምርት መጨመር በዋናነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም የግብርና፣ የማምረቻው እና የማዕድን ዘርፎች አስተዋጽዖ ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዙም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ከአገልግሎት ዘርፍ ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢም እየጨመረ የመጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ ዘርፉ በበጀት ዓመቱ 29 በመቶ ዕድገት አሳይቷልም ነው ያሉት፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በውስጥና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ብታልፍም በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆና መቀጠሏንም ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ተከታታይ አመታት በሃዋላና በመሳሰሉት መንገዶች የሚላከው የውጭ ምንዛሬ በአማካይ 10 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ያነሱት ፕሬዚዳንቷ፥ ባለፈው በጀት ዓመት ከ5 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር በላይ ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል።

ይህም በ2013 ዓ.ም ከተመዘገበው 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር አንጻር በ14 ነጥብ 5 በመቶ በማደግ ባለፉት አስር ዓመታት ተደርሶበት የማይታወቅ መጠን መገኘቱንም ነው ያነሱት፡፡

በታክስ ገቢ ባለፉት አራት ዓመታት የተሻለ ዕድገት መመዝገቡን በመጥቀስም፥ በ2014 ዓ.ም ከአጠቃላይ ዕቅዱ 93 ነጥብ 5 በመቶ አፈጻጸም መመዝገቡንም አመላክተዋል።

በመሰረት አወቀ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.