Fana: At a Speed of Life!

ከህገ-ወጥ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ከ600 በላይ የባንክ ሒሳቦች ታገዱ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከወንጀል ተግባር ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን ከ600 በላይ የባንክ ሂሳቦች ማገዱን አስታወቀ።

አገልግሎቱ ከህገ-ወጥ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ማስተላፍ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 665 የባንክ ሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱን ነው የገለጸው።

የታገዱት የባንክ ሂሳቦች ህጋዊ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ፈቃድ ሳይኖራቸው በህገ-ወጥ መንገድ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ካሉ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር በህገ-ወጥ መንገድ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ናቸው ተብሏል።

በወንጀል ድርጊቶቹ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በህግ ተጠያቂ የማድረግ የተጠናከረ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በመፈፀም የተገኘን ሃብት ከህጋዊ ምንጭና በህጋዊ መንገድ የተገኘ በማስመሰል የመጠቀም ወንጀሎች አፈፃፀም በየጊዜው እየተቀያየረ ያለ ወንጀል ከመሆኑም ባሻገር ከወንጀል ድርጊቶቹ የተገኘው ሃብት ሽብርተኝነትን በገንዘብ በመርዳት ወንጀል መፈፀሚያ ጭምር የሚውል በመሆኑ የመከላከልና መቆጣጠር ስራው በተጠናከረ አግባብ በመከናወን ላይ እንደሚግኝም ተጠቁሟል፡፡

ስለሆነም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎቱ ከባላድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያደርገው ሂደት ህብረተሰቡ መረጃና ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.