Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ስለሺ በሎስ አንጀለስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የአሜሪካ ባለሃብቶች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በሎስ አንጀለስ እና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የአሜሪካ ባለሃብቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም አምባሳደር ስለሺ በኢትዮጵያ ስላሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች እና አጠቃላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።

ባለሃብቶቹ ኢትዮጵያ ገብተው መዋዕለንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች ስራቸው የተቃና ይሆን ዘንድ በመንግስት በኩል ካሁን ቀደም የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት በርካታ የኢኮኖሚ ዘርፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን መወሰዱን አንስተዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ ለረጅም ዓመታት በመንግስት ስር የነበሩ ኩባንያዎችን ወደ ግል ዘርፍ ማሸጋገር፣ እንደ ፋይናንስ፣ ቴሌኮም፣ ኢነርጂ እና መሰል ዘርፎችን የውጭ ባለሃበቶች ገብተው እንዲሰሩ መፈቀድን ለአብነት አንስተዋል።

ከውጭ የሚገባውን የምግብ ነክ አቅርቦት በሀገር ውስጥ አቅም ለመተካት ብሎም ወደ ውጭ ገበያ ለመቀየር እየተሰራ ነው ያሉት አምባሳደሩ÷ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተቀናጀ የስንዴ ምርት ውጤቶች የተያዘው እቅድ እንደሚሳካ አመላካች ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሰፊ የሰው ኃይል፣ አመቺ የአየር ሁኔታ፣ ለገበያ አማካይ የጂኦግራፊ አቀማመጥ፣ ሰፊ የመሬት አቅርቦት፣ በፍጥነት እያደገ የሚገኝ የታዳሽ ኃይል እና መሰል መሰረተ ልማቶች ለባለሃብቶቹ ስራ ስኬት ጉልህ ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል፡፡

በተለይ በአሜሪካ ነዋሪ የዳያስፖራ ወገኖች የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ከኢንቨስትመንት ተሳትፎነቱ ባለፈ ሀገር ይህን ፈታኝ ወቅት በምታልፍበት ወቅት አለኝታነትን ማረጋገጥ እንደሆነም ነው የገለጹት።

በተሳታፊዎቹ በኩል ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ፣ የቢሮክራሲ፣ የመንግስት የፖሊሲ እቅዶች እና ተያያዥ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ባለሃብቶቹ ከመነሻው ጀምሮ ወደ ስራ እስከሚገቡ ድረስ ኤምባሲው ከሀገር ቤት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ላይ በግብርና ልማት፣ በውሃና ኢነርጂ፣ በቴሌኮም፣ በጤና፣ በቡና ልማት፣ በሎጂስቲክስ፣ ፋይናንስ፣ በምርምር እና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች መሳተፋቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.